በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሥልጣንና ተግባር በተሻሻለው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 68 የተመለከተው ይሆናል፤

1) የርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት በተሻሻለው የክልሉ መንግሥት ሕገመንግሥት አንቀጽ 70 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት የክልሉ መስተዳድር እና የርዕሰ መስተዳድር ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ይሆናል፡፡

2) የርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ሥልጣንና ተግባር በተሻሻለው የክልሉ መንግሥት ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 70 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ የተመለከተው ይሆናል፡፡

3) በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ ርዕስ መስተዳደሩ ስልጣንና ተግባሩን ለማከናወን የሚረዱ ልዩ ልዩ ጽህፈት ቤቶችን ሊያቋቁም ይችላል፡፡ ዝርዝሩ በደንብ ይወሰናል፡፡ 

  የክልሉ አጠቃላይ ገፅታ

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 47/1/ ዕውቅና አግኝተው ከተዋቀሩት 11 ክልሎች አንዱ ሲሆን የተዋቀረውም በ1985 ዓ.ም ነው፡፡ ክልሉ በሃገሪቱ ደቡባዊና ደቡብ ምዕራብ የሚገኝ ሲሆን በደቡብ ከኬንያ፣ በደቡብ ምዕራብ ከሱዳን በምዕራብ ከጋምቤላ ክልል እንዲሁም በሰሜን ምዕራብ፣ በሰሜን፣ በምሥራቅና በደቡብ ምሥራቅ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር ይዋሰናል፡፡ የክልሉ የቆዳ ስፋትም 110,931.1 ካሬ ኪ.ሜትር ሲሆን ይህም የሀገሪቱን 1ዐ% የቆዳ ስፋት ይሸፍናል፡፡

የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የሀዋሳ ከተማ አሰተዳደርን ጨምሮ በ18 ዞኖች፣ በ 7 ልዩ ወረዳዎች፣ በ186 ወረዳዎች፣ በ48 የከተማ አስተዳደሮች፣ በ8 ክፍለ ከተሞች እና በ4,221 የገጠርና የከተማ ቀበሌያት የተዋቀረና— 56 ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በጋራ የሚኖሩበት ክልል ነው፡፡ እነዚህ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የኦሞቲክ፣ የኩሽቲክ፣ የኒሎ ሰሀራ እና የሴሜቲክ የቋንቋ ግንድ ቤተሰቦች ናቸው፡፡

በ1999 ዓ.ም በተካሄደው የህዝብ እና ቤት ቆጠራ ውጤት መሠረት የክልሉ ህዝብ ብዛት 16,351,232 ሲሆን በ2012 ዓ.ም የክልሉ ህዝብ ቁጥር 22,130,079 ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህም ከጠቅላላ የሀገሪቱ ህዝብ ብዛት ጋር ሲነፃፀር 2ዐ.1% ይይዛል፡፡  ከክልሉ ህዝብ ውስጥ 17% ብቻ በከተማ የሚኖር ሲሆን 83%ደግሞ በገጠር የሚኖሩ ናቸው፡፡

የክልሉ መንግስት ለህብረተሰቡ ግልጽና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አሣታፊ አሰራርን በማስፈን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ያልተማከለ አሰራርን በመዘርጋት በጀት፣ሥልጣንናየሰው ሃይልን ወደ ታችኛው ዕርከን በማውረድ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

በክልላችን ገጠር አካባቢ የሚገኘው አርሶ አደር ምርትና ምርታማነቱ እንዲጨምር በተደረጉት ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተጠቃሚ እንዲሆን በመደረጉ ኑሮው ተሻሽሏል፣በከተሞችም በተሰሩ የቤቶች ልማት፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም ሌሎች ስራዎች ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ 

በክልሉ የትምህርትን ሥርጭት ተደራሽነት፣ ፍትሀዊነት እና ውጤታማነት የማረጋገጥ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን በተለይም ሽፋንን በማሣደጉ ረገድ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል፡፡ በትምህርቱ ጥራትም ተመሳሳይ ውጤት ለማስመዝገብ የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ፓኬጆች ተቀርፀው ተከታታይነት ያለው ሥራ በመሠራት ላይ ነው፡፡

በመከላከል ላይ የተመሰረተ የጤና ፖሊሲ በመተግበር እንዲሁም የጤና ተቋማትን በማስፋፋትና በማጠናከር የህብረተሰቡን ጤንነት ለመጠበቅ የሚያስችሉ ሰፊ ስራዎች ተከናውነዋል፤ በመከናወን ላይም ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ ባለፉት ዓመታት ህብረተሰቡን የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ተሳታፊና ተጠቃሚ በማድረግ በክልሉ መንግስት ታቅደው በተከናወኑ ዘርፈ-ብዙ ስራዎች ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡

 ተልዕኮ፣ ራዕይ እና እሴቶች

 ተልዕኮ

በክልሉ ያሉትን ሰብአዊና ተፈጥሮአዊ ሐብቶች አቀናጅቶ፣ ቀጣይነት ባለው መልኩ  ጥቅም ላይ እንዲዉሉ በመምራትና በማረጋገጥ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት እድገትን አጠናክሮ በማስቀጠል የክልሉ ህዝብ የልማትና መልካም አስተዳደር ተጠቃሚ  እንዲሆን ማድረግ፡፡

 ራዕይ

በክልሉ ሰላምና ፀጥታ ተረጋግጦ እና መልካም አስተዳደር ሰፍኖ ዘላቂ  ልማትን በማምጣት ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ሆኖ ማየት፡፡

 እሴቶች

· የህግ የበላይነት መርሀችን ነው፡፡

· ለተገልጋይ ፍላጎት ትልቅ ዋጋ እንሰጣለን፣

· መቻቻል ባህላችን ነው፣

· አሳታፊነት መለያችን ነው፡፡

· ፍትሐዊነትና ሚዛናዊነት መመሪያችን ነው፡፡

· ልዩነታችን ውበታችን፣ ውበታችን አንድነታችን ነው፡፡

 

በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት
Organization Type መንግስታዊ
Services
Location ሀዋሳ
Status Active
ContactUs