የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ

ባለፉት ዓመታት በክልላችን የሰላም፣ የዲሞክራሲና የልማት ተግባሮች ለማከናወን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተነደፈው  በብቃት ሊያስፈጸም የሚችል አቅም የተሟላ ሊሆን ባለመቻሉ ከክልል እስከ ቀበሌ በአጠቃላይ የመንግስት መዋቅር የሚታየውን የማስፈጸም አቅም ችግሮችን ለመቅረፍ የአቅም ግንባታ ስትራቴጂዎችንና ፕሮግራሞችን የሚያስተባብርና በበላይነት የሚያስፈጽም ተቋማዊ አካል ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የክልሉን አስፈጻሚና ፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 36/1994 እንደገናም ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 64/95 የአቅም ግንባታ ማስተባበሪያ ቢሮ ሆኖ ሲቋቋም የኢንፎርሚሸን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ከ15 የአቅም ግንባታ ፕሮግራሞች እንደ አንድ አቅም ግንባታ ፕሮግራም ተቀርጾ ሲተገበር ቆይቷል፡፡

ዘርፉ ከ1996 ጀምሮ በቡድን ከዚያም በ1998 በመምሪያ ደረጃ እንዲሁም ከ 2000 ሃምሌ ጀምሮ በስራ ሂደት ሲሰራበት ቆይቷል፡፡ በመቀጠልም በክልሉ የአስፈጻሚ መ/ቤቶችን ለማደራጀትና ስልጣንና ተግባራቸውን ለመወሰን እንደገና በወጣው አዋጅ ቁጥር 127/2002 መሰረት በአቅም ግንባታ ቢሮ ስር  የኢኮቴ ልማት ኤጄንሲ በመሆን የተቋቋመ ሲሆን በመቀጠል በክልሉ የአስፈጻሚ መ/ቤቶችን አደረጃጀቶችና ስልጣንና ተግባራቸውን ለመወሰንና ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 133/2003 መሰረት የክልሉ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኤጄንሲ ሆኖ ተጠሪነቱ ለር/መስተዳደሩ ሆኖ በዚሁ መሠረት ተቋቁሟል፡፡ በመቀጠልም በ2008 ዓ.ም ተጠሪነቱ ለክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ በማድረግ በተሻሻለው የአስፈጻሚ ተቋማት ማቋቋምያ ደንብ ቁጥር ፻፴፮/2ሺ፰ እንዲዋቀር ተደርጓል፡፡  እንዲሁም ቀደም ሲል የቴክኖሎጂ ምርምርና ሽግግር ማዕከል ከተሰጠዉ ተልዕኮ በተጨማሪ የሳይንስና ተክኖሎጂ ተግባራት ታክለዉበት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ልማት ኤጀንሲ በሚል ስያሜ በደንብ ቁጥር 152/2009 እንዲቋቋም ተደርጎ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተግባራትን ሲከውን ቆይቷል ፡፡

በመጨረሻም አሁን በሀገራችን ከመጣው ለውጥ ጋር ተያይዞ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለአገልግሎት አሰጣጥ ምቹ ሆነው እንዲደራጁ በተቀመጠዉ አገራዊ አቅጣጫ መሰረት በክልሉ ምክር ቤት የአስፈጻሚ አካላት ስልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን በወጣዉ አዋጅ ቁጥር 180/2012 በአዲስ መልክ የተቋቋመዉ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ የሚጠበቅበትን ተግባርና ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እንዲችል እንዲሁም ከዚህ ቀደም የኢንፎርሜሽንና ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ እና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ልማት ኢንስቲትዩት ኃላፊነቶችና ተግባራትን በአንድ ላይ በማዋሃድ በቢሮ ደረጃ እንዲደራጅ ሆኗል፡፡

ራዕይ

“በ2030 በክልላችን ውጤታማ የሆኑ የሳይንስና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂዎችን በፍጥነት የመማር፣ የማልማት፤ የመፍጠር፣ የማላመድ እና የመጠቀም አቅም ተገንብቶ ማየት”

ተልዕኮ

ለክልሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ጉልህ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ የሳይንስና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስራዎችን ለህብረተሰቡ በአግባቡ በማልማት፣ በመተግበርና በማስፋት ክልላዊ ብሎም አገራዊ የተወዳዳሪነት አቅምና በቴክኖሎጂ የዳበረ የአሰራር ስርዓት መፍጠር ነዉ፡፡